ጦይባ ሀሰን ዋና ዳይሬክተር
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ ለተጠለሉ ስደተኞች የሚሰጠዉ ሰብአዊ ርዳታካኹን በኃላ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ውጪ ባሉ አካላት እንደሚሰራጭ ተነገረ::
አገልግሎቱ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID ) (WFP) የሚሰጡትን ርዳታ እስካለፈዉ ዓመት አጋማሽ ድረስ የሚያከፋፍለዉ የኢትዮጵያ መንግስት ነበር። ይሁንና ርዳታዉ ተሰርቋል ወይም ላልተፈለገ ዓላማ ዉሏል በሚል ድርጅቶቹ ርዳታ መስጠታቸዉን አቁመዉ እንደነበር ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ኃላፊ ጠይባ ሐሰን ከዚሕ በኋላ ርዳታዉን የሚያሰራጩት ስድስት አለም አቀፍ እና ብሔራዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸዉ ብለዋል።
ጠይባ የድርጅቶቹን ስም ግን አልጠቀሱም። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ዉስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ሠፍረዋል።
በኢትዮጵያ ለተጠለሉት ስደተኞች ይቀርብ የነበረውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለስድስት ወራት ተቋርጦ የቆየ ሰኾን በረሃብ እና ያንን ተከትሎ በተከሰቱ በሽታዎችና ሞት እንደነበርም የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተርዋ ጠይባ ሲናገሩ ተደምጠዋል ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች "የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ" በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጾ ነበረ። "በስደተኞች ካምፖች ውስጥ የከፋ ሰብዓዊ ሁኔታ እና የምግብ አቅርቦት እጥረት እየጨመረ መምጣቱን" ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ መጥቀሱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት
ከዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች በዋናነት ከ ዩ ኤስ ኤይ ዲ ይቀርብ የነበረውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለስድስት ወራት ተቋርጦ በመቆየቱ ኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ውስጥ ባሏት የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉት ስደተኞች ከካምፕ እየወጡ ለችግር እንዲጋለጡ አድርጎ ነበር።
ድጋፉ አሁን የጀመረው መንግሥት ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በምን ጉዳዬች ዙርያ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነው የሚል ከጋዜጠኞች የተነሳላቸው ጥያቄ ዋና ዳይሬክተሯ ጠይባ ሐሰን ሲመልሱ የስርጭት ሥራው በስድስት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች እንዲሰራ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል ውስጥ ከ30 ያላነሱ ስደተኞች በረሃብና በምግብ እጦት መሞታቸውን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ከዚህ በፊት ገልፆ ነበር።
በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ሱዳናዊያን ስደተኞች መካከል ደግሞ ዘጠኝ ያህሉ ምዕራብ ጎንደር ዞን ውስጥ በተቋቋመው የኩመር መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በኮሌራ ወረርሽኝ መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR ) ከሰሞኑ አስታውቆ ነበር ።
የምግብ እርዳታ ለስድስት ወራት ሲቋረጥ የደረሰውን የጉዳት መጠን የጠየቅናቸው ወይዘሮ ጠይባ ቁጥሩ ባይጠቅሱም በረሃብም ፣ በበሽታም የሞቱ እንደነበሩ ግን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። እርዳታው ሙሉ በሙሉ ሲቋረጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ኢትዮጵያን ብለው ለመጡት ስደተኞች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ኃላፊዋ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት እና መሰል ችግሮች ከአገልግሎት ውጪ የሆኑትን ጨምሮ 26 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አሉ። ከተቋሙ ባገኘነው መረጃ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 80 ሺህ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ይኖራሉ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው የትጥቅ ግጭት እና ከጎረቤት ሀገራት ወደ አማራ፣ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ሶማሌ ክልሎች የሚደረገው ስደት በመጠለያ ጣቢያዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መባባስ ምክንያት መሆኑን መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ. ም ባወጣው መግለጫ ገልጿል። በጋምቤላ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር የስደተኞችን ፈተና የበለጠ አባብሶታልም ማለቱ ይታወሳል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በእርዳታ ስርጭት ወቅት ስደተኞች የማይፈልጉት እህል እንዳይቀርብ ለረጂው አካል በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡንና እርዳታው እንዲቋረጥ ምክንያት ሆነው ነበር በተባሉ አጥፊ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግሯል። በቀጣይ ስደተኞች በዘላቂነት በሚኖሩበት መጠለያ አካባቢ በልማት ሥራ ተሰማርተው እንዲኖሩ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ገልጿል።
(ንጋት ፕሬስ)


