ግለ- ታሪክ
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ውስጥ ከሰላሳ አመታት በላይ የሰራ ሰው ነው። በተለያዩ የሚድያ ዘርፎች ተዘዋውሮ ሰርቷል። ቅልጡፍ አእምሮው በተለይም የሙዚቃ እውቀቱ እጅግ የሚደንቅ ሰው ነው። ይኽ ሰው ዘከርያ መሐመድ ይባላል። የንጋት ፕሬስ አርትኦት ክፍል በዚህ ደራሲና ጋዜጠኛ ዙርያ አንዳንድ ነጥቦች ማንሳት ወዷል። ዝርዝር ታሪኩን በዝግታ አንብቡት...
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡
ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡
የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡
በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ዘከሪያ መሀመድ አንዱ ነው፡፡ ዘከሪያ መሀመድ ባለፉት 30 አመታት በቢላል መጽሄት ፤ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኢቲቪ እና በሸገር ያገለገለ ጎልማሳ ነው፡፡ በሳል ተርጓሚና የጥላሁን ገሰሰን ታሪክ ከእነ ሙሉ ክብሩ የጻፋ ነው፡፡ የህይወት ታሪኩን እንድንሰራ ፈቃድ ሰጥቶን እነሆ ብለናል፡፡ የዘከሪያን ታሪክ አይናለም ሀድራና እዝራ እጅጉ ሰንደውታል፡፡
ውልደትና ትምህርት
በጋዜጠኝነት፣ በሕዝብ ግንኙነት፣ በኮሚኒኬሽንና አድቮኬሲ ኦፊሰርነት በጥቅሉ ለ30 ዓመታት ያገለገለው ዘከሪያ መሐመድ ውልደቱና ዕድገቱ አዲስ አበባ ነው።
በመጋቢት ወር 1962 ከአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴ አጠገብ፣ ሚንዳ ሠፈር የተወለደው ዘከሪያ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረው። ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቀ በኋላ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ። በ1984 ከዩኒቨርሲቲው በቴአትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ።
የሥራ ሕይወት
ሁለገቡ ዘከሪያ በብሮድካስትም ሆነ በህትመት ሚዲያ ዘርፍ አበርክቶው ከፍ ያለ ነው። በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና በሸገር FM በተለያዩ ኃላፊነቶች በጋዜጠኝነት አገልግሏል።
ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ወደ ሥራ ዓለም እንደገባ፣ ነጃሺ አሳታሚ ድርጅት ያሳትመው በነበረው ቢላል ወርኃዊ የአማርኛ መጽሔት ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ በምክትል ዋና አዘጋጅነት ሠርቷል፡፡ በዚሁ ጊዜም፣ ከመጽሔት አዘጋጅነቱ በተጓዳኝ በመጻሕፍት ትርጉም እና አርትዖት ላይ ተሳትፏል፡፡
በ1988 ለአንድ ዓመት ገደማ በሕጻናት ቴአትር በስነ- ጽሑፍ ባለሙያነት ካገለገለ በኋላ፣ ከ1989 ጀምሮ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የእንግሊዝኛ ዜና ዴስክ ከረዳት አዘጋጅነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት በድምሩ ለአሥራ አንድ ዓመታት ያህል አገልግሏል፡፡ [በመሃሉ በ1996 አጋማሽ ኢዜኣን ለቅቆ በመውጣት በPerspective ሳምንታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ በዋና አዘጋጅነት ሲሠራ ቆይቶ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1997 አጋማሽ ዳግም ወደ ኢዜአ ተመልሷል፡፡]
በኢዜአ ቆይታው እንደ ጋዜጠኛ በአዲስ አበባ የተካሄዱ በዛ ያሉ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን፣ እና ሁለት ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን (1992 እና 1997) ከመዘገቡ በተጨማሪ፣ ድርጅቱ ላሳተመው “የጋዜጠኝነት ሀሁ” የተሰኘ መጽሐፍ Feature Writing እና Sports Reporting በሚሉ ርዕሶች ጽሑፍ አበርክቷል።
ከባልደረባው መሳይ ምትኩ ጋር ያሰናዱት “A Longway to Peace & Justice” የሚል ርዕስ ያለውና በሁለት ዓመቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ላይ ያተኮረ ባለ 500 ገጽ መጽሐፍ በድርጅቱ ታትሞ ተሰራጭቷል፡፡ በተጨማሪም፣ ኢዜአ በታሕሣሥ 1996 ባሳተመው የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ቅኝት የተሰኘ ሒሳዊ መጽሔት ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የ‹ከሴቶች አድማስ› ዝግጅት ገጽታዎችን የሚቃኝ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡
በ1997/98 መደበኛ ሥራውን በኢዜአ እየሠራ፣ በተደራቢነት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእንግሊዝኛ ዜና ዴስክ ፍሪላንስ የምሽት ዜና ኤዲተር በመኾን ከአንድ ዓመት በላይ ሠርቷል፡፡ በተጨማሪም ዘከሪያ የራዲዮና የቴሌቪዥን ዶኩመንተሪዎችን፣ ጋዜጣ እና መጽሔቶችን በማዘጋጀት ይታወቃል። ከ1996 – 1997 አጋማሽ Perspective የተሰኘ ሳምንታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመኾን ሠርቷል። Perspective ጋዜጣ ዮሐንስ አንበርብር፣ ዮሐንስ የኋላወርቅ እና ዮሐንስ አለነ የተባሉ ወጣቶች ከኮሌጅ ተመርቀው እንደወጡ በሪፖርተርነት በይፋ ሥራ የጀመሩበት፣ እንዲሁም ደራሲና የፖለቲካ ፀሐፊው (Political Commentator) ሙሉጌታ ጉደታ በአምደኝነት የተሳተፈበት ጋዜጣ ነበር፡፡
ዘከሪያ በ2000 ለመጨረሻ ጊዜ ኢዜኣን ለቅቆ በመውጣት፣ ከሙያ ጓደኞቹ ጋር ዛማስ ደቨሎፕመንት ኮሙኒኬሽንስ የሚሰኝ የግል ኩባንያ አቋቋመ፡፡ ኩባንያው ለተለያዩ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በሠራቸው ዶኩመንተሪ ፊልሞች ላይ የድርሻውን አበርክቷል፡፡ ኩባንያው ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋዜጠኞች በይርጋለም፣ ለድሬዳዋ ከተማ ጋዜጠኞች በድሬዳዋ የሰጣቸውን መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ሥልጠናዎች አስተባብሯል፤ በአሠልጣኝነትም ተሳትፏል፡፡
ትርጉም እና አርትዖት (Editing) ዘከሪያ የተካነበት ዘርፍ ነው። የተለያዩ ጽሑፎችን እና የጥናት ውጤቶችን፣ እንዲሁም የዶክመንተሪ ጽሑፎችን ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ፣ እንዲሁም ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተርጉሟል፡፡ በተለያዩ የማጣቀሻ መጻሕፍት እና በዶክመንታሪ ፊልሞች ጽሑፍና ዝግጅት ላይ ሚናው የጎላ ነው።
ፋሲልዳን ኮሙኒኬሽን የተሰኘ ኩባንያ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 የሚጠጉ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ገጽታ የሚያስተዋውቁ ዶኩመንታሪዎች ሲሠራ፣ ዘከሪያ ከ25 በላይ ስክሪፕቶችን በመጻፍ ተሳትፏል፡፡
የሥልጠና ማንዋሎችን ከማዘጋጀት ባሻገር፣ በተለያዩ ግለሰቦች እና የበጎ አድራጎት ተቋማት ለተዘጋጁ ጽሑፎች አርትዖት ሠርቷል። “አብሮ አደግ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የመለሰው ተውኔትም በሜጋ አምፊቲያትር እና በብሔራዊ ቴአትር ለመድረክ በቅቶለታል።
ለሁለት ዓመታት ለአሜሪካ ኤምባሲ የትርጉም ሥራ አገልግሎት የሰጠ ሲኾን፣ በዚሁ ጊዜ ፕሬዚደንት ኦባማ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ ያደረጉትን ታሪካዊ ንግግር እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አካላት ያወጧቸውን ዓመታዊ የሰብኣዊ መብት እና ሌሎች ሪፖርቶችን ጨምሮ፣ በርካታ ጽሑፎችን ተርጉሟል።
ዘከሪያ በ2007 በጋዜጠኞች፣ በሐያሲያን እና በታሪክ ምሁራንም አድናቆት የተቸረውን “ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ይህ መጽሐፍ የጥላሁን ገሠሠን ሕይወት በምልዓት ከመተረክ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ላይ ለሚሠሩ ጋዜጠኞች ዋና ማጣቀሻ በመኾን እያገለገለ ይገኛል፡፡
በሸገር FM በከፍተኛ አዘጋጅነት ለሰባት ዓመታት ያገለገለው ዘከሪያ፣ በቆይታው በሬዲዮ ዶክመንተሪ አዘጋጅነት፣ በዓለም አቀፍ ዜና ተንታኝነት እና በዜና ኤዲተርነት ሠርቷል፡፡ የጣቢያውን የ10ኛ ዓመት በዓል ልዩ መጽሔትም በዋና አዘጋጅነት አሥተባብሮ ለፍሬ አብቅቷል፡፡
ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ዘከሪያ መሐመድ ይህ ጽሑፍ በተሰናዳበት ጊዜ አማና የወጣቶች ልማት ኔትወርክ የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሲኾን፣ በተጓዳኝ የሁለት አንጋፋ ዜጎችን የሕይወት ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛል፡
የዘከሪያ ተመራጭ መጽሐፍ
‹‹……. በእርግጠኝነት የእኔ ተመራጭ መጽሐፍ .... "ቅዱስ ቁርኣን" ነው፡፡ በሸኽ ሰዒድ ሙሐመድ ሳዲቅ እና በሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሀቢብ ተተርጉሞ በ1961 በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት የታተመው የቁርኣን [የፍቺው የአማርኛ] ትርጉም የእኔ የምንጊዜውም ምርጥ ድርሣን ነው። ቁርኣን ባነበብሁት ቁጥር፣ ሁሌም አዲስ ይኾንብኛል፤ ወይም ከዚያ በፊት ያላስተዋልሁት አዲስ ነገር አገኝበታለሁ። በዚህም ምክንያት በእጅጉ እደነቅበታለሁ። ደግሜ ባነበብሁት ቁጥር፣ ከአንዴም ብዙ ጊዜ፣ "ይህን እንዴት እስከዛሬ አላስተዋልሁትም?!" አሰኝቶኛል። በአጻጻፍ ስልቱ ቁርኣንን የሚመስል አንድም መጽሐፍ ዐይቼ አላውቅም።
የቋንቋ ክህሎቴን ያዳበርሁት ደግሞ በዋነኛነት የ1954ቱን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ፣ በተጨማሪም የሀገራችን ታላላቅ የስነ ጽሑፍ ሰዎችን ሥራዎች በማንበብ ነው፡፡,,በማለት ነግሮን ነበር፡፡
ዘከሪያ ሀሣቡን በመቀጠል እንዲህ አለ ፣"ብዙ ሰዎች፣ ሙስሊሞችም ጭምር፣ የ"ተወለደ - አደገ - ጎለመሰ - አረጀ - ሞተ" ዓይነት፣ Beginning, Middle እና End ያለው የትረካ ስልት በመልመዳቸው፣ የቁርአን የፍቺው የአማርኛ ትርጉምን ማንበብ በጣም ይጠናባቸዋል፤ ይከብዳቸዋል። ቁርአን ከአንድ ሡራ [የዩሱፍ (ዮሴፍ) ምዕራፍ] በስተቀር፣ በዚህ ስልት የተዋቀረ አይደለም።"ብሎናል።
...ከተርጓሚዎች ተጨማሪ የማደንቃቸው ግለሰቦችን አስታወስሁ። ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ መስፍን ዓለማየሁ እና ነቢይ መኮንን፣ እንዲሁም የሩስያ ደራሲዎችን ሥራዎች ከሩስኪ የተረጎሙትን ሰዎች።....በማለት ነግሮናል ።
ዘከሪያ ስለሚያደንቀው ሰው
የእኔ Role Model ወይም አርአያ ወደ ጋዜጠኝነት ዓለም እንደገባሁ የተዋወቅሁት ‹‹ጀሚል ከፍልውሃ›› እያለ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ወግ ያቀርብ የነበረው የቢላል መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጀሚል ሸሪፍ ሰዒድ ይመስለኛል፡፡ ልቅም አድርጎ የመጻፍ ዝንባሌዬ ከእርሱ የተወረሰ ይመስለኛል፡፡
(ንጋት ፕሬስ )


