ማህበራዊ /ዜና
ዓለም አቀፉ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤይድ/ በውኃ አቅርቦት፣ በአካባቢና የግል ንጽህና ላይ ትኩረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን ይፋ አደረገ።
ፕሮጀክቶቹ በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበሩ ሲሆን 90 ሚሊየን ዶላር በጀት እንደተያዘላቸው በፕሮጀክቱ ማብሰሪያ መርኃ ግብር ተጠቁሟል።
አንድ ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቁት እነዚህ ፕሮጀክቶች 120 የውኃ፣ ሳኒቴሽንና ንጽህና ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ለማጠናከርም ይሰራሉ ተብሏል።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ውኃ አቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት፣ ክትትልና ግምገማ ማጠናከርና የአቅም ግንባታ ሥራዎች በፕሮጀክቶቹ ትግበራ የሚከወኑ መሆናቸውም ተመላክቷል።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፤ በኢትዮጵያ የውኃና ንጽህና አገልግሎቶችን ለማሳለጥ መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተሰሩ ሥራዎች የተመዘገበ ውጤት ቢኖርም አሁንም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
መንግሥት በነደፈው የ10 ዓመት መሪ ልማት እቅድ ውስጥ በገጠርና ከተማ ያለውን ንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም የውኃ አቅርቦት ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም የጤናና ትምህርት ተቋማት ደኅንነቱ የተጠበቀ ውኃ ማቅረብ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።
በመሆኑም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤይድ/ ይፋ ያደረጋቸው ፕሮጀክቶች በዘርፉ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ አወንታዊ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው ዩ ኤስ ኤይድ በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2016 ጀምሮ 800 ሺህ ዜጎች መሰረታዊ ሳኒቴሽን አገልግሎት ተደራሽ አድርጓል ብለዋል።
200 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ማቅረብ መቻሉን የጠቆሙት አምባሳደር ኤርቪን በኢትዮጵያ አሁንም ብዙ ቁጥር ያለው ዜጋ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ፈላጊ በመሆኑ የበለጠ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ለዚህም የአሜሪካ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋርም እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሰራለን ብለዋል።
"ዛሬ ይፋ ያደረግናቸው ፕሮጀክቶች ለቁርጠኝነታችን ማሳያ ነው፤ ሰዎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ በመሳተፋችን የላቀ ኩራት ይሰማናል" ሲሉም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።
የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤይድ/ ኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የአካባቢ እና የግል ንጽህና/ዋሽ/ ፕሮጀክት አስተባባሪ ደጀኔ ኩመላ በበኩላቸው ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ጥናት በማካሄድ ላይ ነው።
ጥናቱ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ተጠናቆ ፕሮጀክቶቹ ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚሸጋገሩ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ በሁለት ምዕራፍ የተከፈሉ መሆናቸውን ጠቅሰው በከተማ ውኃና አካባቢ ንጽህና ዘርፍ ቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ሃዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ሀረር፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ መቀሌና ባህር ዳር የተመረጡ ከተሞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱና ሀሩራማ አካባቢዎችን የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የውኃ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።
ፕሮጀክቶቹ በሶማሌ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢራዊ ይሆናሉ።
(ንጋት ፕሬስ )


