ቢዝነስ /ዜና
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትን በወርሃ ሐምሌ 2014 ዓ.ም የተቀላቀለዉ አሐዱ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብር 267.7 ሚሊዮን ኪሳራ መድረሱን በሪፖርቱ ገልጧል።
የ 2015 በጀት እና የባንኩን የመጀመሪያዉን ዓመታዊ ሪፖርቱን ባቀረበበት 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባንኩ ከተለያዩ ምንጮች 146.5 ሚሊዮን ብር አጠቀላይ ገቢ ማግኘቱን ገልፆ 414.0 ሚሊዮን ደግሞ ለተቀማጭ ገንዘብ ወለድ፤ ለደመወዝና ለጥቀማጥቅም ወጪ አድርጌያለሁ ያለ ሲሆን በዚህ መነሻነት ባንኩ 267.7 ሚሊዮን ኪሳራ አስመዝግቧል ብሏል።
ካፒታል በተመለከተው ሪፖርት ላይ እንደሚያመላክተዉ የባንኩ የተከፈለ ካፒታሉ 672.6 ሚሊዮን ሲሆን ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ገንዘብ እና 21.6 ሚሊዮን ዶላር የዉጪ ምንዛሬ መሰብሰብ መቻሉን አሳዉቋል።
ጠቅላላ ሀብቴ 3.1 ቢሊዮን ደርሷል ያለዉ አሐዱ ባንክ ከዚህ ዉስጥ 84.2 በመቶ የሚሆነዉ ዕዳ ሲሆን ቀሪዉ 15.8 ፐርሰንት ደግሞ ካፒታል ነዉ ብሏል።
ከ10 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖች የመሰረቱት አሐዱ ባንክ 75 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን በበጀት ዓመቱ በኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ደንበኞች 924.7 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረቡን ገልጧል።
(ንጋት ፕሬስ )
