ጎንደር ዩኒቨርስቲ ከአንድ ግለሰብ በሺዎች የሚቆጠር መጽሀፍ እንደተበረከተለት ተሰምቷል።
መፅሐፎቹን ለእድሜ ጠገቡ ዩኒቨርስቲ ያበረከቱት አበበ ከበደ ይባላሉ።
አበበ ከበደ ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ከተማ ይኖሩ የነበረ ሲኾን በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ታላላቅ ስራዎችን የሰሩ ግለሰብ መኾናቸውን ከታሪካቸው መረዳት ችለናል።
አበበ ከበደ በህይወት ጉዞ ዘመናቸው በተለያዩ የአለም አገራት ሲዘዋወሩ መጻህፍቶችን ይሰበስቡ ነበር።
የመፅሐፍት ርክክብ ሲደረግ
ለመፅሐፍት ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና ስሜት ቤታቸው በውል ለተመለከተው ሰው የአበበ ቤት ጭርስኑ ቤተመፅሐፍ ሊመስለው ይችላል።
አበበ ከበደ ከዚህ ቀደም ትዳርም ኾነ ልጆች ወልደው ለመሳም ያልቻሉበት ምክንያት ልጆቼም ትዳሬም መፅሐፍቶች ናቸው ይሉ እንደነበር በቅርበት የሚያውቋቸው ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ምስክርነታቸው ሰጥተዋል።
አበበ ከበደ ከልጅነት እስከ ህይወት ፍጻሜያቸው ድረስ የሰበሰቧቸውን በርካታ በሺህዎች የሚቆጠሩ መጽሐፎችን የአበበ ከበደ ቤተሰቦች ባሳለፉት ውሳኔ መሠረት ለዕድሜ ጠገቡ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በህዳር 20 ቀን 2016 ዓ/ም የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እና የዩኒቨርስቲው አመራሮች በተገኙበት ሁሉንም መጽሐፎች ማስረከባቸው ሰምተናል ።
በርክክቡ ስነስርአት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት "ይህ አይነት በጎ ተግባር የበለጠ መሥፋት አለበት በሌሎች አለማት ያሉ ባለሀብቶችና አቅም ያላቸው ግለሰቦች ገንዘባቸውን ወጪ እያደረጉ ቤተ መጻህፍት እየሰሩ ለዩኒቨርስቲዎች ያስረክባሉ በእኛ ሀገር ይሕ አልተለመደምና መለመድ ያለበት ተግባር ነው" ሲሉ ተደምጠዋል ።
ዶክተር አስራት አክለውም "የተሰጠን እነዚህ በርካታ መጽሀፍ ለትውልድ የሚጠቅም እና ተማሪዎቻችንን ሊያግዝ የሚችል ነው ለዚህ ስጦታ የአቶ አበበን ቤተሰቦችና ጓደኞች ከልብ እናመሠግናለን፤ የአቶ አበበን ነፍስም በአጸደ ገነት ያኑርልን" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እንዲህ ያለውን መልካም ተግባር መለመድ ያለበት ነው።
(ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)


