ዜና/ቢዝነስ
የኛ ምርት ባዛርና ኤግዚቢሽን ከታህሳስ 03 እስከ 07 2016 ዓ/ም ድረስ ተከፍቶ የሚቆይ ሲኾን፣ በዝግጅቱ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ፣ የፕራና ኤቨንትስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ነብዩ ለማና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስትና የግል የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት መከፈቱን ተመልክተናል።
በመክፈቻ ስነ ስርአቱም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርም "መንግሥት ከያዛቸው የአምስት አመት የልማት ዕቅድ ስትራቴጂዎች የኢንዱስትሪ ዘርፍ አንዱ መኾኑን" አንስተዋል ።
መላኩ አክለውም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በአገር ምጣኔ ሀብት እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰው እነኚህ ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቷቸው ምርቶችንም የአገር ልጆች እንዲጠቀሙባቸውና አለፍ ሲልም የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲኾኑ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ እያደረገ ይገኛል ሲሉ ተደምጠዋል ።
የግሉ ዘርፍ ያሉ ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሳተፍባቸው የሚያስፈልግ መኾኑንና እንደ ፕራና ኤቨንትስ ያሉ ኩባንያዎችንም እንዲበራከቱ ያስፈልጋል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።
የኛ ምርት ባዛርና ኤግዚቢሽን በአገር ውስጥ ያሉ አምራች ኢንተርፕራይዞችና የመንግሥት የልማት አጋር ድርጅቶች የሚሳተፉበት "ኢትዮጵያ ታምርት፣ እኛ እንሸምት" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ነው ተብሏል።
ዝግጅቱ "የኛ ምርት" የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
የኛ ምርት ባዛርና ኤግዝቢሽን ዋና አላማ በምርት ትውውቅ፣ ገበያ ትስስር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በልምድና መረጃ ልውውጥ የተሻለ አቅም መፍጠርና ዘርፉ የለመ ሲኾን እግረ መንገዱም ዘርፉ ያለበትን እድገት ለማሳየት መኾኑን ለማወቅ ችለናል።
የመንግሥት የስራ ሐላፊዎቹ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን በተገኙበት የመክፈቻ መድረክ "ዝግጅቱ ተወዳዳሪ የኾኑ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር ውጥን ያለው መኾኑን ሲናገሩ ሠምተናል።
ባዛሩና ኤግዝቢሽኑ ማዘጋጀቱ አስፈላጊ የኾነበት ምክንያት ሲናገሩ እንደሰማነው የውጭ ምንዛሪ ማስገኘትን ጨምሮ ወደ ውጭ አገራት የሚላኩትን የአገር ውስጥ ምርቶችን ይበልጥ ለማስተዋወቅና ማበረታታት ጨምሮ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማስተዋወቅ ለአገር ምጣኔ ሀብት የሚሰጡት ጥቅም ለማሳደግ ውጥን ያለው ነው ።
በስካይ ላይት ሆቴል ለሶስት ቀናት ተከፍቶ የሚቆየው ይኸው ባዛርና ኤግዚብሽን በአገራቀፍ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲኾን ከ100 በላይ በጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ፣ ኬሚካል፣አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ አምራቾች የሚሳተፉበት መኾኑንም የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ ሲናገሩ ሰምተናል ። በመርኃ ግብሩ ላይ ከ50,000 ያህል ገዥዎችና ጎብኚዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይገመታል።
ባዛሩና ኤግዚቢሽኑ ለማዘጋጀት በአገራቀፍ ደረጃ ከ15 በላይ ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ለውድድር ቀርበው ባስገቡት ንድፈ ሐሳብ መሠረት የተጫረቱ ሲኾን በተደረገው ልየታ መሠረት ፕራና ኤቨንት የተሰኘው አገር በቀል ኩባንያ ባቀረበው ፕሮፖዛል ብቁ ሁኖ በመገኘቱ ዝግጅቱን እንዲያዘጋጅ ፍቃድ ሊሰጠው መቻሉን የኢንተርፕራይዝ ልማት ድርጅት ዳይሬክተሩ አለባቸው ንጉሴ መናገራቸውንም ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኃላፊው አለባቸው አክለው እንዳብራሩት ፕራና ኤቨንትስ ባለው ልምድ ፣የቴክኒክ ብቃትና ገንዘብን አብቃቆቶ በመጠቀም ደረጃ ባለው የካበተ ልምድ መሠረት ለአምስት ቀናት በስካይ ላይት ሆቴል የሚከናወነውን ባዛርና ኤግዚቢሽን ይሁንታ እንዲያዘጋጅ ሊሰጠው መቻሉንም በወቅቱ በተገኘንበት ጋዜጣዊ መግለጫ ከኃላፊው ንግግር ለመረዳት ችለናል ።
በመርሐግብሩ ጎን ለጎን በዘርፉ ያሉ ችግሮች እንደ የምርት ቅቡልነት ችግር፣ የአምራች ኢንተርፕራይዞች በምጣኔ ሐብቱ ላይ ያላቸው ሚና፣ የፋይናንስ አቅርቦት ዙርያ የመንግሥት ሐላፊዎች፣ ምጣኔ ሀብት አከናዋኞች እንዲኹም የዘርፉ ሙሁራን በተገኙበት ውይይት ይደረጋል ተብሏል።
የፕራና ኤቨንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነብዩ ለማ በበኩላቸው ባዛሩና ኤግዚቢሽኑን አስመልክተው ለንጋት ፕሬስ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ በሌሎች አገራት ያለውን ልምድ ጠቅሰው ፣ እንዲህ ያለውን ባዛርና ኤግዚሸን ዝግጅት ማዘጋጀቱ አምራች ኢንተርፕራይዞች በአገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መኾኑን አፅንኦት ነግውረናል።
ነብዩ ለማ በማብራርያቸው፣ በተለይም መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አብዝተው ከሚፈተንባቸው መካከል የግብአት፣ ገበያና የሰው ኃይል አቅርቦት ለመፍታትና ችግር ለመፍታት ብሎም በአገር ውስጥ ያሉ አምራቾች የገበያ ትስስር በመፍጠር ከፍተኛ እገዛ በመፍጠር ለዘርፉ እድገት የራሱን ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በበጀት አመቱ ከያዛቸው መሠረታዊ ዕቅዶች መካከል ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ የመተካት ውጥን ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንዳለም ዳይሬክተሩ አለባቸው ንጉሴ ሲናገሩ ሰምተናል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአኹን ላይ ከ26 ሺህ በላይ አነስተኞና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በመላው አገሪቱ ይገኛሉ ተብሏል። በተቋሙ መሪ ልማት ዕቅድ እንደተጠቀሰውም ከፍተኛ ካፒታልና የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ ሚጠይቀው ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በማሸጋገር ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መኾኑን በመረጃው ተጠቅሷል።
በተያዘው በጀት አመትም ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ አሁን ላይ ከደረሰችበት የውጭ ምንዛሪ የገቢ ደረጃ 405.6 ቢልየን ወደ 900 ቢልየን ለማድረስ ውጥን ይዛ እየተንቀሳቀሰች መኾኑን ከኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ሰምተናል።
(ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)