ዜና/ማሕበራዊ
ምስል: የማስታወቅያ ማሕበሩ ውይይት ሲያደርጉ
አዲስ አበባ (ንጋት ፕሬስ) - በአዲስአበባ ከተማ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአደባባይ ማስታወቅያ በተመለከተ የወጣውን ሕግ ያልተወያየንበትና የኢንዱስትሪውን ባህሪ ያላገናዘበ ነው ሲል የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ባለሞያዎች ማህበር ሕጉን ወቅሷል ።
የማስታወቅያ ማህበሩ ይህንን ሲናገር የሰማነው መጋቢት 04 ቀን 2016 ዓ/ም በአዲስአበባ ሃያት ሪጀንሲ ሆቴል ባካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው።
የማስታወቂያ ማህበሩ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን መስርያ ቤት በበመዲናይቱ አዲስአበባ ከተማ የሚሰቀሉ የአደባባይ ማስታወቅያዎችና ቢልቦርዶችን መሉ በሙሉ በዲጂታል መቀየር ይኖርባቸዋል የሚል መመርያ ማውጣቱን ተከትሎ ባለሞያዎቹ ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛል።
የከተማ መስተዳድሩ "አዲስአበባን ውብ እንደስሟ የሚል ዘመቻ" መጀመሩን ተከትሎ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያስከተለ መኾኑን የገለፀው ማህበሩ፣ ከነኝህ ዘርፎች መካከልም "የማስታወቂያ ስራ ላይ የተሰማራን ባለሞያዎችና ድርጅቶች ከፍተኛ ችግር ደቅኖብናል" ሲሉ ተቃውሞ እያቀረቡ መኾኑን ለመታዘብ ችለናል።
ባለስልጣኑ ከባለፈው አመት ጀምሮ በአደባባይ የሚሰቀሉ ማስታወቅያዎችን በተመለከ ጥናት አከናውኛለኹ ያለ ሲኾን ከእንግዲህ በኃላ ዲጂታል ማስታወቂያዎች በስተቀር በከተማው ባነሮችን ማየት አልፈልግም ማለቱን ተከትሎ፣ የማስታወቅያ ማህበሩ ባለስልጣኑ አስጠናኹት ያለውን ጥናት የከተማዋ እድገት ያልተከተለና የማስታወቅያ ኢንዱስትሪው ባህሪ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ሲል በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል ባካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ የባለስልጣኑ ውሳኔ ላይ ወቅሳ ሲያቀርብ ሰምተናል።
በዚሁ ዙርያ ከንጋት ፕሬስ ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረጉት የማህበሩ አባል አክያ ተሾመ እንደነገሩን "ለመኾኑ ዲጂታል እናድረገው ቢባልም እንዃ በከተማዋ ያለውን የመብራት መቆራረጥ ችግር ጋር ተያይዞ የማስታወቅያ ስራ ላይ እንቅፋት አይኾንም ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ"።
የአክያ ማስታወቅያ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አክያ ተሾመ አክለውም፣ ይኽን ውሳኔ የማስታወቅያ ኢንዱስትሪው የተሸከመው የስራ እድልና የሰው ኃይል እንዲቀንስ የሚያደርግ በመኾኑ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ መፍጠሩ አይቀርም ሲሉ ይሞግታሉ። እንዲህ ያለውን ተሞክሮም በአገራችን ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ተህዋሲ ወረርሺን መከሰቱ ጋር ተያይዞ በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል በከፍተኛ ኹኔታ እንደጎዳው ነግረውናል።
በርካታ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ባለሞያዎች ማህበር የአዲስ አበባ ከተማ የከተማውን ማስታወቂያ ለማዘመን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደ ባለድርሻ አካል ምክረ-ሀሳብ ለመስጠት እና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ላይ በውይይቱ ላይ ሀሳቦችን አንስቷል ።
በአዲስአበባ ከተማ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣንና ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የአደባባይ ማስታወቅያዎችን በተመለከተ በጋራ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከ2016 በጀት አመት ጀምሮ የማስታወቂያ ሕጉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግሮ የነበረ ቢኾንም እስካሁን ግን ሕጉ ተግባራዊ አልተደረገም።
በመግለጫው ተገኝተን እንደሰማነው ከኾነም የማስታወቅያ ማህበሩ በአዲስአበባ ከተማ የሚሰቀሉ የአደባባይ ማስታወቅያዎች ዲጂታል እንዲኾኑ ከማስታወቂያ ባለሞያዎች ማህበር ጋር ከስምምነት እንደተደረሰበት ተናግሮ የነበረ ቢኾንም፣ ማህበሩ ግን በዚኹ ዙርያ ከመንግስት አካላት ጋር ያደረግኩት ውይይትም ኾነ የደረስኩበት ስምምነት የለም ሲል በጠቅላላ ጉባኤው ሲናገር ተደምጧል ።
በአዲስ አበባ ሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በተካሔደው ጠቅላላ ጉባኤው ላይም የአዲስአበባ ከተማ መስተዳድር የሚመለከታቸው የመንግሥት የስራ ሐላፊዎች እንዲገኙ ተጋብዘው የነበረ በኾንም በጉባኤው ላይ ሳይገኙ እንደቀሩ ከኢትዮጵያ ማስታወቅያ ባለሞያዎች ማህበር ሰምተናል ።
( ለንጋት ፕሬስ አማኑኤል ክንደያ)