"ፈረጃ" የተሰኘውን የህዝብ ፊልም ለመስራት ዝግጅት መጀመሩን ሰምተናል

 ዜና/ኪን



                የፈረጃ ፊልም ሰሪዎች (ፎቶ ሲሳይ ጉዛይ)


ኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያግዝ እንቅስቃሴ ተጀመረ


ኢትዮጵያውያን ፊልም ሰሪዎች የአገር ውስጥ ፊልም ለማሳደግ ደፋ ቀና ማለት መጀመራቸውን ተሰምቷል።


ከህዝብ ሐብትን በማሰባሰብና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ የሚያኖርበት ፊልም ያስፈልጋል በሚል እንቅስቃሴዎች ከተጀመረ ዋል አደር ቢልም ውጥኑ ወደ ፍፃሜው ተቃርቦ ለኢትዮጵያዊያን ለእይታ ሊቀርብ ነው።


የፊልሙ ርዕስ "ፈረጃ" ይሰኛል።


" ፈረጃ " የሚል ስያሜ ያገኘው ይኸው ፊልም አጠቃላይ ለመስራት ከሶስት ሚሊዮን ብር መዋእለ ንዋይ ይጠይቃል ተብሏል።


የፊልሙ ደራሲ በተለያዩ ፊልሞች በመተወን የሚታወቀው አርቲስት ሔኖክ ወንድሙ ነው።




ፊልሙ ሮዝ ኢንተርቴመንት፣ ከኢነርጂ ፊልም ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበር የሚሰራ መኾኑን አዘጋጆቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አውቀናል።


 "ፈረጃ" የተሰኘውን ፊልም ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ይፈጃል ከመባሉ በተጨማሪም ፣ ፊልሙ በአይነቱ የተለየ ይዘት ያለው መኾኑን አዘጋጆቹ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ/ም በአዲስ አበባ ቤልቪው ሆቴል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን መግለጫና ማብራርያ ሰጥተዋል።


ለፊልሙ ስራ ይውል ዘንድ እስካሁን 2.6 ሚሊየን ብር  ለመሰብሰብ መቻሉንም የሃሳቡ አመንጪ  አርቲስት ሄኖክ ወንድሙ ለመገናኛ ብዙሐን እወቁት ብሏል።


"ፈረጃ" ፊልምን ሰርቶ ለማጠናቀቅ የተወጠነለት በጀት 3,175,000 ብር ሲሆን 754 ሺ ብር ይቀረዋል መባሉን ሰምተናል ።


የፊልም ስራ ኃሳብ አመንጪው አርቲስት ሔኖክ ወንድሙ በዚህ ወር መጨረሻ የተዋናዮች ምልመላና ልየታ እንደሚጀምር ሲናገር ተደምጧል።




ሔኖክ እንደተናገረው "ፈረጃ" የተሰኘውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ አመት ግድም ጊዜ  ይጠይቃል ።


ይኽን ፈረጃ የተሰኘውን ፊልም ከፊልም አፍቃርያን የተሰበሰበና በህዝብ ሐብት የተሰራ የመጀመርያው ፊልም ያደርገዋል ተብሏል።


በኢትዮጵያ ያለውን የፊልም ስራ ጥበብ መጓተትና የኢንዱስትሪው እድገት መንቀራፈፍ የዝግጅት እጥረትና የባለሞያዎች ችግር እጦት እንደኾነ በምክንያትነት ሲጠቀስ ቆይቷል።


ሌላኛው እንደችግር የሚነሳው የትብብርና የምርምር ችግር እንደኾነ ሲነገር ይሰማል።


ይኸው "ፈረጃ " የተሰኘው ፊልም  ይኽንንኑ ችግር ለመቅረፍ ማሳያ ተደርጎ መወሰድ እንደሚችል አዘጋጆቹ እምነት እንዳላቸው ሲናገሩ ሰምተናል።


"ፈረጃ" ፊልም ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት የሚያሳርፈው አዎንታዊ ሚናን ጨምሮ አሁን ላይ ያለውን የፊልም ስራ አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ እንደሚያግዝ በአዲስ አበባ ከተሰጠው መግለጫ ተረድተናል ።


[ለንጋት ፕሬስ  አማኑኤል ክንደያ]