ዜና/ ቢዝነስ
ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ድርጅቶችና ተቋማት በምርትና አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ያሉበትን ደረጃ በቂ አለመሆኑን የገለፀ ሲኾን በርካታ መሻሻል ያለባቸው ዘርፎች መኖራቸውን አስታውቋል።
በተለይም ድርጅቱ ካለው ግምገማ አንፃር ከሚያመርቷቸው ምርቶችና በሚሰጡት አገልግሎት ረገድ በአህጉራቀፍና አለማቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚያርችል ነው ብሎ እንደማያምን የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ መብራት ተናግረዋል።
ቴዎድሮስ መብራት አክለውም የምርት ደረጃቸውን ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ልህቀት እንዲደርሱ የሚያስችላቸውን ስራዎች መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።
ድርጅቱ በየ አመቱ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የአገር ውስጥ ተቋማት እየሸለመ እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈው አመትም በአገልግሎት ዘርፍ ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታልን፣ በምርት ዘርፍ ደግሞ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር የሚገኝ ተቋማትን መሸለሙ ተናግሯል።
የካቲት 11 - 2017 ዓ/ም በአዲስአበባ ከተማ ስካይ ላይት ሆቴል አመታዊ ጉባኤ የተከናወነ ሲሆን በጉባኤው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታውና ከተለያዩ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የተውጣጡ ተቋማት ተገኝተዋል።
በጉባኤው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደተናገሩት በአገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስሪዎችና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትብብር የመስራቱ ነገር እየተስተዋለ እንዳልሆነ አንስተዋል።
ዶክተር ሳሙኤል፣ በሌሎች አለማት ያሉ ኢንዱስትሪዎች እየተጓዙበት ያለውን ልምድ ጠቅሰው በኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን ተግባር እምብዛም እየተተገበረ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲበረቱና የኢንዱስትሪ ዘርፍ የእውቀት ሽግግር እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ግዜያቶችም መንግስት የትኩረት አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
በመረኃ ግብሩ ከተሳተፉትና ባለፈው አመት የጥራት ደረጃ መለክያ ብልጫ ያመጡ የግል ተቋማት ያላቸውን ልምድ ያጋሩ ሲሆን ተቋማት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ ለውጤት የሚያበቃቸው ስትራቴጂ 'እንዴት መከተል አለባቸው' በሚለው ዙርያ ገለፃ ማድረጋቸውን ታዝበናል።
በኢትዮጵያ ያሉ ኢንዱስትሪዎችና የእውቀት ሽግግር ክፍተት አስመልክተው ጥናታቸውን ያቀረቡት ደግሞ በአዲስአበባ ዮኒቨርስቲ የኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ሲሆኑ በመንግሥት ፓሊሲዎችና በድርጅቶች በመካከል ያልተሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በዚህ ረገድ ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን በጥናታቸው አንስተዋል።
ፕሮፌሰር ዳንኤል፣ በተለይም የዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎችና የኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ተቋማት በትብብር የሚሰሩበት ሁኔታ አለመፈጠሩ ዘርፉ ወደ ኃላ እንዲቀር እንዳደረገው ካላቸው የዘርፉ ልምድና ተሞክሮ አንፃር ትዝብታቸውን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቃለመጠይቅ ተናግረዋል ።
ተቋማት የምርትና አገልግሎት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ለሀገሪቱ እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠቃሚ ናቸው ያሏቸውን ምክረ- ኃሳቦችንም ፕሮፌሰር ዳንኤል ሲናገሩ ሰምተናል።
በመድረኩ ላይ የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን በዘርፉ እንደክፍተት የሚነሱ ጉዳዮች በተመለከተ የቀድሞ የአዲስአበባ ንግድና የዘርፉ ማሕበራት ምክርቤት ፕሬዝዳንት መሰንበት ሽንቁጤ አወያይነት ሐሳቦችና አስተያየቶች ተሰጥቶባቸዋል ።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ያዘጋጀው የኸው መድረክ "በልህቀት ሞዴል አማካኝነት የጥራት ባሕልን ማሳደግ" በሚል መሪ ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የተቋቋመው በ2000 ዓ/ም ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ያሉ ድርጅቶች የልህቀት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ መቆየቱን የሚታወቅ ነው።
ይሄኛው መርኃ ግብርና መድረክ ሲዘጋጅ ለ3ኛውን ዙር ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት እንደነበር ተመልክተናል።
የሀገሪቱን አለም አቀፍ የተወዳዳሪነት ብቃት ማሳደግ እና የጥራት ፅንሰ ሐሳብን በማስረፅ ጥራት የሀገሪቱ ባህል እንዲሆን ማገዝን ያለመ መሆኑንም ተገልጿል።
በአማኑኤል ክንደያ
Advertisements