ዜና/ኪን
አድዋ በሚገባው ልክ አልተዘከረም አልተወደሰም ብለው የሚሞግቱ በርካቶች ናቸው።
የአድዋ ድል በአል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ያጎናፀፈው ፀጋና በረከት ከፍተኛ ቢኾንም ጥቅሙን ለኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፓለቲካዊ ጉዳዮች የሰጠው ጥቅም እምብዛም ነው።
የአድዋ ድል በአልን ለኢትዮጵያና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የሰጠው ጥቅም ከሚሟገቱ መካከል የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የፊልም መምህሩ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ቀዳሚው ነው ማለት ይቻል ይሆናል።
ኃይሌ ድሉን ኪነጥበባዊ ለዛውና አጠቃላይ ክንዋኔው ገልፆ አይጠግበውም፣ በፊልም በኩልም ይዞ ለመምጣት ከፍተኛ ጥቶች እያደረገ ያለ ሲሆን [40 years later the adwa children's] በውጥን ደረጃ ያለ የኪነጥበብ ስራው ነው።
በሌላ በኩል፣ ኪነጥበብ ለአድዋ ድል የነበረው አስተዋፅኦ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ሲገልፁ ድሉ ድራማዊ ነበር ሲሉ የጥበብ ከፍታን የኢትዮጵያ ታሪክ መፅሐፋቸው ላይ ጠቅሰውታል። ይሁንናው ዘመናት ሲተካኩ እዚኽ ላይ ደርሰናል።
ላለፉት ስምንት አመታት ዝክረ አድዋ ኢትዮጵያዊነት የተሰኘ የጥበብ ዝግጅት በብሔራዊ ትያትር ቤት በርካቶች ታድመዋል ተጋብዘዋል።
በመጪው ዓርብ 'ለት የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም በአድዋ ሙዝየም በደማቁ ተዘጋጅቶ እንደሚከበር የዝክረ አድዋ ኢትዮጵያዊነት አዘጋጅ ጋዜጠኛና የመድረክ አስተዋዋቂ አብርሃም ግዛው ገልጿል።
አብርሃም ግዛም አድዋን በየአመቱ በመዘከር፣ እንዲከበር በማድረግና የድሉን ዋጋ እንዲታወስ በማድረግ ረገድ የደከመ ባለሞያ ሲሆን የዘንድሮው በአድዋ ሙዝየም ተከብሮ እንዲውል አንድ ደረጃ ከፍ አድርጎታል ማለት ይቻላል።
"ዝክረ አድዋ ኢትዮጵያዊነት" የተሰኘውን ይኸው ልዩ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ፣ በመጪው አርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በአድዋ ሙዚየም የሚጀመር መሆኑን ዛሬ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን ከተሰጠው መግለጫ መረዳት ችለናል።
ዝግጅቱ በአብርሃም ግዛው ኢንተርቴይንመንት ኃ.የተ.የግ. ማሕበር የሚያከናውነውና በአድዋ ድል ዋዜማ በሚካሄደው በዚህ የኪነጥበብ መርሃ ግብር በርከት ያሉ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተሰናድቷል ተብሏል።
"ኢትዮጵያዊነት ዝክረ አድዋ" በሚል ጥናታዊ ፅሁፍና ዲስኩር [የመድረክ ንግግር] በምሁራን የሚቀርብበት፣ የግጥም ምሽትና ኮሜዲም አይነቶች እንደሚቀርቡበት መረዳት ችለናል።
በተጨማሪም፣ ፖለቲከኞች በሰላምና አንድነት ዙሪያ አነቃቂ ንግግሮች የሚያደርጉ ሲሆን አርበኞች ሽለላና ፉከራ በባህላዊ ባንድ ታጅበው የሚያቀርቡበት መሆኑን ተነግሯል።
ደራሲ፣ ገጣሚና ፀሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱን ጨምሮ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ዶ/ር ወዳጄነህ ማህረነ፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ መምህር ዲያቆን ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ፣ መጋቢ ቸርነት በላይነህ (ፓስተር ቸሬ)፣ አርቲስት ተስፋዬ ሲማ፣ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን ብሎም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት በሆነው የአድዋ ድል ዋዜማ ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙ ሲሆን መግብያ ትኬቱን መደበኛ 300 ብር እንዲሁም ለቪ አይ ፒ ደግሞ 500 ብር መሆኑን ከኢንተርቴመንቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ትኬቱን በቴሌብር መተግበርያ ላይ መቁረጥ የሚቻል ሲሆን በአካል ደግሞ ጃዕፈር መፅሐፍ ቤትና 2 ሺ አበሻ ባህላዊ ሬስቶራንት መገኛው ነው ተብሏል።
በአማኑኤል ክንደያ
ADVERTISEMENTS